1 “አንተ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ የሸክላ ጡብ ወስደህ ከፊት ለፊትህ አስቀምጥ፤ የኢየሩሳሌምን ከተማ ካርታ ሥራበት።
2 ከዚያም በወታደር እንደሚከበብ ክበባት፤ ምሽግ ሥራባት፤ ዐፈር ደልድልባት፤ ጦር ሰፈሮችን ቀብቅብባት፤ ቅጥር መደርመሻ ግንዶችንም በዙሪያዋ አስቀምጥባት።
3 የብረት ምጣድ ወስደህ በአንተና በከተማዪቱ መካከል እንደ ብረት ቅጥር አቁመው፤ ፊትህንም ወደ እርሷ አዙር፤ የተከበበች ትሆናለች፤ አንተም ትከባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል።
4 “አንተ በግራ ጐንህ ተኛ፤ የእስራኤልም ቤት ኀጢአት በአንተ ላይ ይሁን፤ በዚህ ጐንህ በተኛህበት ቀን ቊጥር ኀጢአታቸውን ትሸከማለህ።
5 እነርሱ ኀጢአት ባደረጉባቸው ዓመታት መጠን የቀን ቊጥር መድቤብሃለሁ። ስለዚህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን የእስራኤልን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ።