1 እኔም በልቤ፣ “መልካም የሆነውን ለማወቅ፣ በተድላ ደስታ እፈትንሃለሁ” አልሁ፤ ነገር ግን ያም ከንቱ ነበረ።
2 ደግሞም፣ “ሣቅ ሞኝነት ነው፤ ተድላ ደስታስ ምን ይጠቅማል?” አልሁ።
3 አሁንም አእምሮዬ በጥበብ እየመራኝ ራሴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት፣ ሞኝነትንም ለመያዝ ሞከርሁ፤ ሰዎች በአጭር የሕይወት ዘመናቸው ከሰማይ በታች ባለው ላይ ቢሠሩት ሊጠቅማቸው የሚችል ምን እንደሆነ ለማየት ፈለግሁ።
4 ታላላቅ ነገሮችን አከናወንሁ፤ ለራሴ ቤቶችን ሠራሁ፤ ወይንንም ተከልሁ፤
5 አትክልትን ተከልሁ፤ የመዝናኛ ስፍራዎችን አዘጋጀሁ፤ በእነዚህም ላይ ፍሬ የሚያፈሩ የዛፍ ዐይነቶችን ሁሉ ተከልሁባቸው፤