1 በጽዮን መለከትን ንፉ፤በቅዱሱ ተራራዬም የማስጠንቀቂያውን ድምፅ አሰሙ፤በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፤እርሱም በደጅ ነው።
2 ይህም የጨለማና የጭጋግ ቀን፣የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው።የንጋት ብርሃን በተራሮች ላይ እንደሚወጣ፣ኀያልና ብዙ ሰራዊት ይመጣል፤ከጥንት እንዲህ ዐይነት ከቶ አልነበረም፤በሚመጡትም ዘመናት እንዲህ ዐይነት ከቶ አይሆንም።
3 በፊታቸው፣ እሳት ይባላል፤በኋላቸውም ነበልባል ይለበልባል፤በፊታቸው ምድሪቱ እንደ ዔድን ገነት ናት፤በኋላቸውም የሚቀረው ባዶ ምድረ በዳ ነው፤ምንም አያመልጣቸውም።
4 መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፤እንደ ጦር ፈረስም ይጋልባሉ።
5 ገለባ እንደሚበላ እንደሚንጣጣ እሳት፣ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ኀያል ሰራዊት፣የሠረገሎችን ድምፅ የሚመስል ድምፅ እያሰሙ፣በተራሮች ጫፍ ላይ ይዘላሉ።