3 አምላካችሁ እግዚአብሔር ስለ እናንተ ሲል በእነዚህ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረገውን ማናቸውንም ነገር እናንተው ራሳችሁ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋላችሁ ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነው።
4 ከዮርዳኖስ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ በሙሉ ካሸነፍኋቸው ሕዝቦች ያልወረሳችሁትን ቀሪ ምድር ርስት እንዲሆን ለየነገዶቻችሁ እንዴት አድርጌ በዕጣ እንዳከፋፈልኋችሁ አስታውሱ።
5 ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ከፊታችሁም ያሉበትን ስፍራ ያስለቅቃቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁም ተስፋ መሠረት ምድራቸውን ትወርሳላችሁ።
6 “በርቱ፤ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳትሉ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ለመጠበቅና ለማድረግ እጅግ በርቱ።
7 በመካከላችሁ ከቀሩት ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር አትተባበሩ፤ የአማልክቶቻቸውን ስም አትጥሩ፤ አትማሉባቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትስገዱላቸውም፤
8 ነገር ግን እስካሁን እንዳደረጋችሁት ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አጥብቃችሁ ያዙ።
9 “እግዚአብሔር ታላላቅና ኀያላን ሕዝቦችን ከፊታችሁ አሳድዶ አስወጥቶአቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ማንም ሊቋቋማችሁ አልቻለም።