2 “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ የሚለው ይህ ነው፤ “ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ ምድር በምትገኘው በኢየሩሳሌምም ለእርሱ ቤተ መቅደስ እንድሠራ አዞኛል።
3 ከሕዝቡ መካከል በእናንተ ዘንድ የሚኖር ማናቸውም ሰው አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣና በዚያ ለሚኖረው አምላክ፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ይሥራ፤
4 ባሉበት ስፍራ የሚቀሩ በየትኛውም አገር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስጦታ እንዲሆን በበጎ ፈቃድ ከሚያቀርቡት መባ በተጨማሪ ብርና ወርቅ፣ ዕቃና እንስሳ በመስጠት ይርዷቸው።’ ”
5 ከዚያም እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው የይሁዳና የብንያም ቤተ ሰብ አለቆች እንዲሁም ካህናቱና ሌዋውያኑ ሁሉ ለመሄድና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት ተዘጋጁ።
6 ጎረቤቶቻቸውም ሁሉ በበጎ ፈቃድ ከሰጡት መባ በተጨማሪ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎችን፣ ቈሳቍስን፣ እንስሶችንና ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ ስጦታዎችንም በመለገስ ረዷቸው።
7 ከዚህም በላይ ንጉሡ ቂሮስ፣ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤተ ጣዖት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንዋያተ ቅድሳት አወጣ።
8 የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በግምጃ ቤቱ ኀላፊ በሚትሪዳጡ አማካይነት ንዋያተ ቅድሳቱ እንዲመጡና በይሁዳው ገዢ በሰሳብሳር ፊት እንዲቈጠሩ አደረገ።