1 አብራም ሚስቱንና ንብረቱን ሁሉ ይዞ ከግብፅ ወደ ኔጌብ ሄደ፤ ሎጥም አብሮት ነበረ።
2 አብራም በከብት፣ በብርና በወርቅ እጅግ በልጽጎ ነበር።
3 አብራም ከኔጌብ ተነሥቶ እስከ ቤቴል ተጓዘ፤ ቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳኑን ከተከለበት፣
4 ለመጀመሪያ ጊዜም መሠዊያ ካቆመበት ስፍራ ደረሰ፤ በዚያም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠራ።
5 ከአብራም ጋር አብሮት ይጓዝ የነበረው ሎጥ በጎች፣ ከብቶችና ድንኳኖች ነበሩት።
6 ሆኖም ሁለቱ አንድ ላይ ሲኖሩ ስፍራው አልበቃቸውም፤ ንብረታቸው እጅግ ብዙ ስለ ነበር፣ አብረው መኖር አልቻሉም።
7 ይህም በመሆኑ በአብራምና በሎጥ እረኞች መካከል ጠብ ተፈጠረ። በዚያን ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያው አገር ይኖሩ ነበር።