2 ባያቸውም ጊዜ፣ “ይህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰፈር ነው” አለ፤ የዚያንም ቦታ ስም መሃናይም አለው።
3 ያዕቆብም በኤዶም አገር ሴይር በተባለው ምድር ወደሚኖረው ወንድሙ ወደ ዔሳው መልእክተኞችን አስቀድሞ ላከ፤
4 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፤ “ጌታዬን ዔሳውን እንዲህ ትሉታላችሁ፤ ‘አገልጋይህ ያዕቆብ እንዲህ ብሎአል በሉት፤ “ከላባ ዘንድ ተቀምጬ እስከ አሁን ድረስ እዚያው ኖርሁ፤
5 ከብቶች፣ አህዮች፣ የበግና የፍየል መንጎች እንደዚሁም የወንድና የሴት አገልጋዮች አሉኝ፤ አሁንም ይህን መልእክት ለጌታዬ መላኬ በጎ ፈቃድህን እንዳገኝ በማሰብ ነው።”
6 የተላኩትም ሰዎች ወደ ያዕቆብ ተመልሰው፣ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ሊቀበልህ በመምጣት ላይ ነው፤ አራት መቶ ሰዎችም አብረውት አሉ” አሉት።
7 ያዕቆብም በታላቅ ፍርሀትና ጭንቀት ተውጦ፣ አብረውት የነበሩትን ሰዎች ሁለት ቦታ ከፈላቸው፤ በጎቹን ፍየሎቹን ከብቶቹንና ግመሎቹንም ሁለት ቦታ ከፈላቸው፣
8 “ዔሳው መጥቶ በአንደኛው ላይ አደጋ ቢጥል፣ ሌላው ክፍል ሊያመልጥ ይችላል” ብሎ አስቦ ነበር።