20 የይሁዳና የእስራኤል ሕዝቦች ብዛታቸው እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ሆነ፤ ይበሉ፣ ይጠጡና ይደሰቱም ነበር።
21 ሰሎሞንም ከወንዙ አንሥቶ እስከ ፍልስጥኤማውያን ምድር፣ ከዚያም እስከ ግብፅ ዳርቻ ያሉትን መንግሥታት ሁሉ ገዛ፤ እነዚህም አገሮች ግብር አመጡለት፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ተገዙለት።
22 ለሰሎሞን በየቀኑ የሚገባለትም ቀለብ ይህ ነበር፤ ሠላሳ ኮር ማለፊያ ዱቄት፣ ሥልሳ ኮር መናኛ ዱቄት፣
23 ዐሥር ቅልብ ሰንጋዎች፣ ሃያ ግጦሽ መሬት ላይ የሚውሉ በሬዎች፣ መቶ በግና ፍየል እንዲሁም ዋሊያ፣ ሚዳቋ፣ የበረሓ ፍየልና ምርጥ አዕዋፍ።
24 ከወንዙ በስተ ምዕራብ፣ ከቲፍሳ እስከ ጋዛ ያሉትን መንግሥታት ስለ ገዛ፣ በሁሉም አቅጣጫ ሰላም ሆኖለት ነበር።
25 በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ከዳን አንሥቶ እስከ ቤርሳቤህ ያለው ይሁዳና እስራኤል፣ እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ ጥላ ሥር በሰላም ለመኖር በቃ።
26 ሰሎሞን ሠረገላ የሚጐትቱ ፈረሶች የሚያድሩበት አራት ሺህ ጋጣና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶች ነበሩት።