18 ከዚያም ኢዩ ሕዝቡን ሁሉ በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አለ፤ “አክዓብ በኣልን ያገለገለው በጥቂቱ ነው፤ ኢዩ ግን ይበልጥ ያገለግለዋል።
19 አሁንም የበኣልን ነቢያት ሁሉ አገልጋዮቹንና ካህናቱንም በሙሉ ጥሩልኝ። ለባኣል ትልቅ መሥዋዕት ስለማቀርብ አንድ ሰው እንኳ እንዳይቀር። የማይመጣ ሰው ቢኖር ግን በሕይወት አይኖርም፤ ኢዩ ግን ይህን ማድረጉ የበኣልን አገልጋዮች ለማጥፋት ተንኰል መፍጠሩ ነበር።
20 ኢዩም፣ “ለበኣል ክብር ጉባኤ ጥሩ” አለ፤ እነርሱም ይህንኑ ለሕዝቡ አስታወቁ።
21 ከዚያም በመላው እስራኤል መልእክት ላከ፤ የበኣል አገልጋዮች በሙሉ መጡ፤ ማንም አልቀረም፤ ሁሉም ወደ በኣል ቤተ ጣዖት ገቡ፤ የበኣል ቤተ ጣዖት ዳር እስከ ዳር ሞላ።
22 ኢዩም የልብስ ቤቱን ኀላፊ፣ “ለበኣል አገልጋዮች ሁሉ አልባሳት አውጣ” አለው፤ እርሱም አልባሳቱን አወጣላቸው።
23 ከዚያም ኢዩ ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ጋር ወደ በኣል ቤተ ጣዖት ገባ። የበኣልንም አገልጋዮች፣ “እንግዲህ የበኣል አገልጋዮች ብቻ እንጂ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እዚህ አብረዋችሁ አለመኖራቸውን አረጋግጡ” አላቸው።
24 ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት ለማቅረብ ገቡ። በዚህ ጊዜም ኢዩ፣ “በእጃችሁ አሳልፌ ከሰጠኋችሁ ሰዎች አንድ እንኳ እንዲያመልጥ ያደረገ በገመዱ ይገባበታል” ብሎ በማስጠንቀቅ ውጭ ሰማንያ ሰዎች አዘጋጅቶ ነበር።