5 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ዳዊትና ዘሮቹ በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንዲነግሡ በጨው ኪዳን የሰጣቸው መሆኑን አታውቁምን?
6 የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባሪያ የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን በጌታው ላይ ዐመፀ።
7 የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም ገና ሕፃን ሳለ፣ ምንም ማድረግ በማይችልበትና እነርሱንም ለመቋቋም አቅሙ በማይፈቅድለት ጊዜ የማይረቡ ጥቂት ወሮበሎች በዙሪያው ተሰበሰቡበት፣ በረቱበትም።
8 “አሁንም እናንተ በዳዊት ዘርዐ-ትውልድ እጅ ያለውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልትቋቋሙ አስባችኋል። በእርግጥም በሰራዊት ረገድ እጅግ ብዙ ናችሁ፤ አማልክቶቻችሁ ይሆኑ ዘንድ ኢዮርብዓም የሠራቸውንም የወርቅ ጥጆች ይዛችኋል።
9 ደግሞስ የአሮን ልጆች የሆኑትን ካህናትና ሌዋውያን አባርራችሁ፣ ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ እናንተም የራሳችሁን ካህናት አልሾ ማችሁምን? አንድ ኮርማና ሰባት አውራ በግ ይዞ ራሱን ለመቀደስ የሚመጣ ማናቸውም ሰው አማልክት ላልሆኑ ለእነዚያ ጣዖታት ካህን ይሆናል።
10 “ለእኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱንም አልተውንም፤ እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ ያሉት ካህናት የአሮን ልጆች ሲሆኑ፣ ረዳቶቻቸውም ሌዋውያኑ ናቸው።
11 እነርሱም በየጧቱና በየማታው የሚቃጠል መሥዋዕትና ሽታው ደስ የሚያሰኝ ዕጣን ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፤ የገጹን ኅብስት በሥርዐቱ መሠረት በነጻው ጠረጴዛ ላይ ያኖራሉ፤ በየማታውም በወርቁ መቅረዝ ላይ ያሉትን ቀንዲሎች ያበራሉ፤ እኛም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንፈጽማለን፤ እናንተ ግን ትታችሁታል።