7 እላችኋለሁ፤ እንደዚሁም ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ፣ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።
8 “ወይም ዐሥር የብር ሳንቲሞች ያላት ሴት ከዐሥሩ አንዱ ቢጠፋባት፣ እስክታገኘው ድረስ መብራት አብርታ፣ ቤቷን ጠርጋ፣ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት?
9 ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆቿንና ጐረቤቶቿን፣ በአንድነት ጠርታ፣ ‘የጠፋብኝን የብር ሳንቲም አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ትላቸዋለች።
10 እላችኋለሁ፤ እንደዚሁም ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።
11 ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት።
12 ከእነርሱም ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‘አባቴ ሆይ፤ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው፤ አባትየውም ሀብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው።
13 “ብዙም ቀን ሳይቈይ፣ ታናሹ ልጅ ድርሻውን ሁሉ ጠቅልሎ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም በማጋጣነት ንብረቱን አባከነ።