19 ማርያም ግን ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር።
20 እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።
21 ስምንት ቀን ሆኖት የመገረዣ ጊዜው ሲደርስ፣ ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተባለ።
22 በሙሴ ሕግ መሠረት፣ የመንጻታቸው ወቅት በተፈፀመ ጊዜ፣ ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ወጡ፤
23 ይኸውም በጌታ ሕግ፣ “ተባዕት የሆነ በኵር ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ለመፈጸምና
24 ደግሞም በጌታ ሕግ፣ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፣” መሥዋዕት ለማቅረብ ነበር።
25 በዚያን ጊዜ ጻድቅና ትጒሕ የሆነ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው በኢየሩሳሌም ይኖር ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን መጽናናት የሚጠባበቅና መንፈስ ቅዱስ በላዩ ያደረሰው ነበር።