9 ሰባቱ የመጨረሻ መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፣ “ና፤ የበጉ ሚስት የሆነችውን ሙሽራ አሳይሃለሁ” አለኝ።
10 በመንፈስም ወደ አንድ ትልቅና ረጅም ተራራ ወስዶኝ፣ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ።
11 እርሷም በእግዚአብሔር ክብር ታበራ ነበር፤ የብርሃኗም ድምቀት እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ፣ እንደ መስተዋት የጠራ ነበር።
12 ዐሥራ ሁለት በሮች የነበሩት ትልቅና ረጅም ቅጥርም ነበራት፤ በበሮቹም ላይ ዐሥራ ሁለት መላእክት ቆመውና የዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ስም ተጽፎ ነበር።
13 በምሥራቅ ሦስት በሮች፣ በሰሜን ሦስት በሮች፣ በደቡብ ሦስት በሮች፣ በምዕራብ ሦስት በሮች ነበሩ።
14 የከተማዪቱም ቅጥር ዐሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩት፤ በእነርሱም ላይ የዐሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።
15 ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ የከተማዪቱን በሮች ቅጥር የሚለካበት የወርቅ ዘንግ ነበረው።