6 ደግሞም በዙፋኑ ፊት እንደ መስተዋት የጠራ የብርጭቆ ባሕር ነበረ።በዙፋኑ መካከል፣ በዙሪያውም ከፊትና ከኋላ በዐይን የተሞሉ አራት ሕያዋን ፍጡራን ነበሩ።
7 የመጀመሪያው ሕያው ፍጡር አንበሳ፣ ሁለተኛው በሬ ይመስሉ ነበር፤ ሦስተኛው የሰው ፊት የሚመስል ፊት ነበረው፤ አራተኛው ደግሞ የሚበር ንስር ይመስል ነበር።
8 አራቱም ሕያዋን ፍጡራን እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት ክንፎች ነበሯቸው፤ በዙሪያቸውና በውስጣቸው በዐይኖች የተሞሉ ነበሩ፤ ቀንና ሌሊትም፦“ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣የነበረው፣ ያለውና የሚመጣው፤ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ”ማለትን አያቋርጡም።
9 ሕያዋን ፍጡራኑ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ከዘላለም እስከ ዘላለም ሕያው ሆኖ ለሚኖረው ክብር፣ ሞገስና ምስጋና በሚሰጡበት ጊዜ፣
10 ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ፊት ተደፍተው፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ሕያው ሆኖ ለሚኖረው ይሰግዱ ነበር፤ አክሊላቸውንም በዙፋኑ ፊት አስቀምጠው እንዲህ ይላሉ፤
11 “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ሆነዋልምና።”