1 ነገሥት 7:1-7 NASV

1 ሰሎሞን የራሱን ቤተ መንግሥት ሠርቶ ለመጨረስ ዐሥራ ሦስት ዓመት ወስዶበታል፤

2 የሊባኖስ ዱር የተባለ ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ይህም ርዝመቱ መቶ ክንድ፣ ወርዱ አምሳ ክንድ፣ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ ሲሆን፣ በአራት ረድፍ የቆሙ የዝግባ ምሰሶዎች ደግፈው የያዟቸው አግዳሚ የዝግባ ተሸካሚዎች ነበሩት።

3 ቤቱ ከምሰሶዎቹ ላይ ያረፉ አግዳሚ ተሸካሚዎች አሉት፤ በእያንዳንዱ ዐምድ ላይ ዐሥራ አምስት፣ በድምሩ አርባ አምስት ተሸጋጋሪዎች ሲኖሩ፣ ከእነዚህም ተሸጋጋሪዎች በላይ ከዝግባ የተሠራ የጣሪያ ክዳን ነበር።

4 መስኮቶቹም ከፍ ብለው የተሠሩ በሦስት ምድብ የተከፈሉና ትይዩ ነበሩ።

5 በሮቹ በሙሉ ባለ አራት ማእዘን መቃኖች ያሏቸው፣ በሦስት ምድብ የተከፈሉና ትይዩ ነበሩ።

6 ሰሎሞን፣ “ባለ ብዙ ምሰሶ አዳራሽ” የተባለ ቤት ሠራ፤ የዚህም ርዝመቱ አምሳ ክንድ፣ ወርዱ ሠላሳ ክንድ፣ ነበር፤ በስተ ፊት በኩልም ጣራ ያለውና በአዕማድ የተደገፈ መመላለሻ ነበረው።

7 ዳኝነት የሚያይበትንም የዙፋን ችሎት አዳራሽ ሠራ፤ ይኸውም የፍትሕ አዳራሽ የተባለው ነው፤ ይህንንም ከወለሉ አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ ሳንቃ ሸፈነው።