1 ዜና መዋዕል 17:2-8 NASV

2 ናታንም ለዳዊት፣ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለ ሆነ፣ ያሰብከውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት።

3 በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጥቶ እንዲህ አለው፤

4 “ሂድና ለባሪያዬ ለዳዊት እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ እኔ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም።

5 እስራኤልን ከግብፅ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ከአንዱ ድንኳን ወደ ሌላው ድንኳን፣ ከአንዱ ማደሪያ ወደ ሌላው ማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ፣ በቤት ውስጥ አልኖርሁም።

6 ከእስራኤላውያን ጋር በሄድሁባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ሕዝቤን እንዲጠብቁ ላዘዝኋቸው መሪዎቻቸው ከቶ፣ “ለምን ከዝግባ ዕንጨት ቤት አልሠራችሁልኝም ያልሁበት ጊዜ አለን?”

7 “እንግዲህ አሁንም ለባሪያዬ ለዳዊት እንዲህ ብለህ ንገረው፤ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘የሕዝቤ የእስራኤል ገዥ እንድትሆን በጎችን ከመጠበቅና ከመከተል አንሥቼ ወሰድሁህ።

8 በሄድህበት ሁሉ ከአንተ አልተለየሁም፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስምህን እንደ ምድር ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ።