1 ከዚህ በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው፤ በቍጥጥሩም ሥር አዋላቸው፣ ሜቴግ አማ የተባለችውንም ከተማ ከፍልስጥኤማውያን ቍጥጥር ነጻ አደረጋት።
2 እንዲሁም ዳዊት ሞዓባውያንን ድል አደረገ፤ በመሬት ላይ አጋድሞ በገመድ ለካቸው፤ በገመድ ከተለኩትም ሁለት እጅ ሲገድል፣ አንድ እጅ ግን በሕይወት ይተው ነበር። ስለዚህ ሞዓባውያን የዳዊት ተገዦች ሆኑ፤ ገበሩለትም።
3 ከዚህም በቀር ዳዊት በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ያለውን ግዛት መልሶ ለመያዝ በሄደ ጊዜ፣ የሱባን ንጉሥ የረአብን ልጅ አድርአዛርን ወጋው።
4 ዳዊትም አንድ ሺህ ሠረገሎች፣ ሰባት ሺህ ፈረሰኞችና ሃያ ሺህ እግረኞች ማረከበት። ቊጥራቸው መቶ የሆነ የሠረገላ ፈረሶች ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹን በሙሉ ቋንጃቸውን ቈረጠ።
5 የደማስቆዎቹ ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ለመርዳት በመጡ ጊዜ ዳዊት ሃያ ሁለት ሺህ ሰው ገደለባቸው።