2 ሳሙኤል 8:1-6 NASV

1 ከዚህ በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረጋቸው፤ በቍጥጥሩም ሥር አዋላቸው፣ ሜቴግ አማ የተባለችውንም ከተማ ከፍልስጥኤማውያን ቍጥጥር ነጻ አደረጋት።

2 እንዲሁም ዳዊት ሞዓባውያንን ድል አደረገ፤ በመሬት ላይ አጋድሞ በገመድ ለካቸው፤ በገመድ ከተለኩትም ሁለት እጅ ሲገድል፣ አንድ እጅ ግን በሕይወት ይተው ነበር። ስለዚህ ሞዓባውያን የዳዊት ተገዦች ሆኑ፤ ገበሩለትም።

3 ከዚህም በቀር ዳዊት በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ያለውን ግዛት መልሶ ለመያዝ በሄደ ጊዜ፣ የሱባን ንጉሥ የረአብን ልጅ አድርአዛርን ወጋው።

4 ዳዊትም አንድ ሺህ ሠረገሎች፣ ሰባት ሺህ ፈረሰኞችና ሃያ ሺህ እግረኞች ማረከበት። ቊጥራቸው መቶ የሆነ የሠረገላ ፈረሶች ብቻ ሲቀሩ ሌሎቹን በሙሉ ቋንጃቸውን ቈረጠ።

5 የደማስቆዎቹ ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ለመርዳት በመጡ ጊዜ ዳዊት ሃያ ሁለት ሺህ ሰው ገደለባቸው።

6 ከዚያም የደማስቆ ክፍል በሆነው የሶርያውያን ግዛት የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ። ሶርያውያን ተገዙለት፤ ገበሩለትም። እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድልን ሰጠው።