2 ነገሥት 22:14-20 NASV

14 ካህኑ ኬልቅያስ፣ አኪቃም፣ ዓክቦርና፣ ሳፋን፣ ዓሳያም የሐርሐስ የልጅ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የአልባሳት ጠባቂውን የሴሌምን ሚስት ነቢዪቱን ሕልዳናን ለመጠየቅ ሄዱ። እርሷም የምትኖረው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ሰፈር ነበር።

15 ነቢዪቱም፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤

16 “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ በዚህ ቦታና በሕዝቡ ላይ አመጣለሁ።

17 እኔን ስለተውኝና ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑ፣ እጆቻቸው በሠሯቸውም አማልክት ሁሉ ስላስቈጡኝ፣ ቊጣዬ በዚህ ቦታ ላይ ይነዳል፣ አይጠፋምም።’ ”

18 እግዚአብሔርን እንድትጠይቁ ወደዚህ ቦታ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ይህን ንገሩት፣ ‘ስለ ሰማኸው ነገር የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤

19 “ለርግማንና ለጥፋት የተዳረጉ ስለ መሆናቸው በዚህ ቦታና በሕዝቡ ላይ የተናገርኩትን ስትሰማ ልብህ ስለ ተነካና ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ስላዋረድህ፣ ልብስህንም ቀደህ በፊቴ ስላለቀስህ እግዚአብሔር ሰምቼሃለሁ ብሏል።

20 ስለዚህ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ ወደ መቃብር በሰላም ትወርዳለህ፤ በዚህ ቦታም የማመጣውን መከራ ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ” ሰዎቹም መልሱን ለንጉሡ ይዘውለት ሄዱ።