5 ንጉሥ ሰሎሞንም ሃያ ሁለት ሺህ በሬ፣ መቶ ሃያ ሺህ በግና ፍየል ሠዋ፤ ንጉሡና ሕዝቡም ሁሉ በዚህ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቀደሱ።
6 ካህናቱም እንደ ሌዋውያኑ፣ ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔር እንዲወደስበት የሠራውንና “ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት እግዚአብሔርን ባመሰገነ ጊዜ የተቀመጠበትን የእግዚአብሔርን የዜማ መሣሪያ ይዘው በተመደበላቸው ስፍራ ቆሙ። ካህናቱ በሌዋውያኑ ትይዩ ሆነው መለከቶቻቸውን ሲነፉም እስራኤላውያን ሁሉ ቆመው ነበር።
7 ሰሎሞን የሠራው የናስ መሠዊያ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህሉን ቊርባንና ስቡን መያዝ ስላልቻሉ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ያለውን የመካከለኛውን አደባባይ ክፍል ቀድሰው፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ በዚያ አቃጠለ።
8 በዚያን ጊዜ ሰሎሞን ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ጋር ለሰባት ቀን በዓሉን አከበረ፤ ሕዝቡም ከሐማት መግቢያ እስከ ግብፅ ወንዝ ድረስ ካለው ምድር የመጣ እጅግ ታላቅ ጉባኤ ነበር።
9 መሠዊያውን ለሰባት ቀን ስለ ቀደሱና የሰባት ቀን በዓል በተጨማሪ ስላከበሩ፣ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አደረጉ።
10 ሰሎሞንም በሰባተኛው ወር፣ በሃያ ሦስተኛው ቀን ወደየቤታቸው እንዲሄዱ ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔር ለዳዊትና ለሰሎሞን እንዲሁም ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው በጎ ነገር ሁሉ በልባቸው ደስ እያላቸውና ሐሤት እያደረጉ ሄዱ።
11 ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሥራ ጨረሰ፤ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለራሱ ቤተ መንግሥት ያደርግ ዘንድ በልቡ ያሰበውን ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣