ዘፀአት 10:14-20 NASV

14 እነርሱም ግብፅን በሙሉ ወረሩ፤ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሆነው የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሁሉ አለበሱ። እንዲህ ያለ የአንበጣ መዓት ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ ወደ ፊትም ደግሞ አይኖርም።

15 ምድሩ ሁሉ ጠቍሮ እስኪጨልም ድረስ አለበሱት። ከበረዶ የተረፈውን በመስክ ላይ የበቀለውንና በዛፍ ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ፣ ጠርገው በሉ። በግብፅ ምድር ሁሉ በዛፍ ላይ ወይም በተክል ላይ አንዳች ቅጠል አልተረፈም ነበር።

16 ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ያህዌ) በእናንተም ላይ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤

17 እንግዲህ አሁን አንድ ጊዜ ደግሞ ኀጢአቴን ይቅር በሉኝና ይህንን ቀሣፊ መዓት እንዲያስወግድልኝ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለምኑልኝ።”

18 ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ።

19 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ነፋሱን ወደ ብርቱ የምዕራብ ነፋስ ለወጠው ያም ነፋስ አንበጣዎቹን እየነዳ ወደ ቀይ ባሕር ከተታቸው፤ በግብፅ ምድር በየትኛውም ቦታ አንድም አንበጣ አልቀረም።

20 እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን እንዲሄዱ አልፈቀደም።