8 አብርሃምም እርጎ፣ ወተትና የተዘጋጀውን የጥጃ ሥጋ አቀረበላቸው፤ ሲበሉም ዛፉሥር አጠገባቸው ቆሞ ነበር።
9 እነርሱም አብርሃምን፣ “ሚስትህ ሣራ የት አለች?” ብለው ጠየቁት።እርሱም፣ “ድንኳን ውስጥ ናት” አላቸው።
10 እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ በእርግጥ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው።ሣራም በዚህ ጊዜ ከበስተ ጀርባው ካለው ከድንኳኑ ደጃፍ ሆና ትሰማ ነበር።
11 በዚያን ጊዜ አብርሃምና ሣራ አርጅተው፣ ዕድሜአቸው ገፍቶ ነበር፤ ሣራም ልጅ የመውለጃዋ ዕድሜ ዐልፎ ነበር።
12 ሣራ በልቧ፣ “ካረጀሁና ጌታዬም ከደከመ በኋላ በዚህ ነገር መደሰት ይሆንልኛል?” ብላ ሣቀች።
13 እግዚአብሔርም (ያህዌ) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሣራ፣ ‘ካረጀሁ በኋላ ልጅ እንዴት አድርጌ እወልዳለሁ’ ስትል ለምን ሣቀች?
14 ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት በተባለው ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሣራም ልጅ ይኖራታል።”