20 ነገር ግን ለእግዚአብሔር መልስ የምትሰጥ አንተ ማን ነህ? “ሥራ ሠሪውን፣ ‘ለምን እንዲህ ሠራኸኝ?’ ይለዋልን?”
21 ሸክላ ሠሪ፣ ከሚሠራው ጭቃ፣ አንዳንዱን ሸክላ ለክብር፣ ሌላውን ደግሞ ለተራ አገልግሎት የማድረግ መብት የለውምን?
22 እግዚአብሔር ቊጣውን ለማሳየት፣ ኀይሉንም ለማሳወቅ ፈልጎ የቍጣው መግለጫ የሆኑትን፣ ለጥፋትም የተዘጋጁትን እጅግ ታግሦ ቢሆንሳ!
23 አስቀድሞ ለክብር ላዘጋጃቸው፣ የምሕረቱም መግለጫዎች ለሆኑት፣ የክብሩ ባለጠግነት እንዲታወቅ ይህን አድርጎ እንደሆነስ?
24 የጠራው ከአይሁድ ወገን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብ ወገን የሆነውን እኛን እንኳ ሳይቀር አይደለምን?
25 በሆሴዕ እንዲህ እንደሚል፤“ሕዝቤ ያልሆኑትን፣ ‘ሕዝቤ’ ብዬ እጠራቸዋለሁ”፤ያልተወደደችውንም ‘የተወደደችው’ ብዬ እጠራለሁ።
26 ደግሞም፣ “ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’፤ተብሎ በተነገራቸው በዚያ ቦታ፣‘የሕያው እግዚአብሔር ልጆች’ ተብለውይጠራሉ።”