5 ምንም በሥጋ ከእናንተ ርቄ ብገኝ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና በሥርዐት መኖራችሁንና በክርስቶስ ያላችሁን ጽኑ እምነት እያየሁ ደስ ይለኛል።
6 እንግዲህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት እንዲሁ በእርሱ ኑሩ፤
7 በእርሱ ተተክላችሁና ታንጻችሁ፣ እንደ ተማራችሁት በእምነት ጸንታችሁ፣ የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረባችሁ ኑሩ።
8 በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ልማድና በዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።
9 የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በእርሱ ይኖራልና፤
10 እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል።
11 በእርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ፤