9 ከእኔ የተማራችሁትን ወይም የተቀበላችሁትን፣ የሰማችሁትን ወይም ያያችሁትን ማናቸውንም ነገር አድርጉ፤ የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።
10 ከብዙ ጊዜ በኋላ በአዲስ መንፈስ ስለ እኔ ማሰብ በመጀመራችሁ፣ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በርግጥ በተግባር ለመግለጽ ዕድሉ አልነበራችሁም እንጂ ማሰቡንስ ታስቡልኝ ነበር።
11 ይህን የምለው ስለቸገረኝ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን፣
12 ማጣትን ዐውቀዋለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብም፣ ባገኝም ሆነ ባጣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ።
13 ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ።
14 ሆኖም የመከራዬ ተካፋይ ስለ ሆናችሁ መልካም አድርጋችኋል።
15 ከዚህም በላይ፣ እናንተ የፊልጵስዩስ ሰዎች ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ በመጀመሪያ ወንጌልን በተቀበላችሁ ጊዜ ከመቄዶንያ ስነሣ፣ ከእናንተ በቀር በመስጠትና በመቀበል የትኛውም ቤተ ክርስቲያን አልተባበረም።