10 ዳዊትም፣ “አባትህ ክፉ ቃል ቢመልስልህ ማን ይነግረኛል?” ብሎ ጠየቀው።
11 ዮናታን፣ “በል ና፤ ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው፤ ተያይዘውም ወጡ።
12 ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ምስክር ይሁንብኝ፤ አባቴን ነገ መርምሬ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በዚህ ሰዓት እልክብሃለሁ፤ ስለ አንተ ያለው አመለካከት በጎ ከሆነም አሳውቅሃለሁ።
13 ነገር ግን አባቴ ክፉ አስቦብህ፣ ይህን ሳላሳውቅህ ብቀርና በሰላም እንድትሄድ ባላደርግ፣ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፤ ከዚያም የባሰ ያምጣብኝ። እግዚአብሔር ከአባቴ ጋር እንደ ነበር እንደዚሁ ከአንተም ጋር ይሁን።
14 አንተም እኔ በሕይወት እስካለሁ ድረስ እንዳልገደል የእግዚአብሔርን በጎነት አድርግልኝ።
15 እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ ከምድረ ገጽ በሚደመስስበት ጊዜ እንኳ የበጎነት ሥራህ ከቤተ ሰቤ በፍጹም አይቋረጥ።”
16 ስለዚህ ዮናታን፣ “የዳዊትን ጠላቶች እግዚአብሔር ይፋረዳቸው” በማለት ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።