37 ነግቶ የወይን ጠጁ ስካር ካለፈለት በኋላ የሆነውን ሁሉ ስትነግረው ልቡ ቀጥ አለ፤ ሰውነቱም እንደ ድንጋይ በድን ሆነ።
38 ዐሥር ቀን ያህል ካለፈ በኋላ፣ እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፤ እርሱም ሞተ።
39 ዳዊትም ናባል መሞቱን በሰማ ጊዜ፣ “የናባልን ስድብ የተበቀለልኝና እኔን አገልጋዩን ክፉ ከማድረግ የጠበቀኝ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ናባል የሠራውንም ክፉ ነገር በራሱ ላይ መለሰበት” አለ።ዳዊትም አቢግያ ሚስት ትሆነው ዘንድ በመጠየቅ መልእክት ላከባት።
40 አገልጋዮቹም ወደ ቀርሜሎስ ሄደው አቢግያን፣ “ሚስት ትሆኚው ዘንድ እንድንወስድሽ ዳዊት ወደ አንቺ ልኮናል” አሏት።
41 እርሷም ተነሥታ በግምባሯ በመደፋት እጅ ከነሣች በኋላ፣ “እነሆ፤ እኔ ገረድህ አንተን ለማገልገል፣ የጌታዬንም አገልጋዮች እግር ለማጠብ ዝግጁ ነኝ” አለች።
42 አቢግያም ወዲያውኑ በአህያ ላይ ተቀምጣ አምስት አገልጋዮቿን በማስከተል፣ ከዳዊት መልእክተኞች ጋር ሄደች፤ ለዳዊትም ሚስት ሆነችው።
43 እንዲሁም ዳዊት ኢይዝራኤላዊቷን አኪናሆምን አገባ፣ ሁለቱም ሚስቶቹ ሆኑ።