1 ሚስቶች ሆይ፤ እናንተም እንደዚሁ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ አንዳንድ ለቃሉ የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው አኗኗር ተማርከው ይመለሳሉ፤
2 ይህም የሚሆነው ንጹሕና ፍጹም አክብሮት የተሞላውን ኑሮአችሁን ሲመለከቱ ነው።
3 ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በመሽሞንሞን ይኸውም ሹሩባ በመሠራት፣ በወርቅ በማጌጥና በልብስ አይሁን፤
4 ነገር ግን ውበታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፣ ገርና ጭምት መንፈስ ያለበት፣ ምንጊዜም የማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት ይሁን።
5 ተስፋቸውን በእግዚአብሔር ላይ የጣሉ የቀድሞ ቅዱሳት ሴቶች ራሳቸውን ያስዋቡት በዚህ ዐይነት ለባሎቻቸው በመገዛት ነበርና።
6 ሣራም አብርሃምን “ጌታዬ” እያለች ትታዘዘው ነበር፣ እናንተም ምንም ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ የእርሷ ልጆች ናችሁ።
7 ባሎች ሆይ፤ እናንተም ደግሞ ጸሎታችሁ እንዳይደናቀፍ በኑሮአችሁ ሁሉ ለሚስቶቻችሁ አስቡላቸው፣ ደካሞች ስለሆኑና የሕይወትንም በረከት አብረዋችሁ ስለሚወርሱ አክብሯቸው።