2 ቆሮንቶስ 10:1-7 NASV

1 እኔ ጳውሎስ፣ በእናንተ ፊት ስሆን “ዐይነ ዐፋር”፣ ከእናንተ ስርቅ ግን፣ “ደፋር” የተባልሁ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እለምናችኋለሁ።

2 ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ በዓለማዊ መንገድ እንደምንኖር አድርገው በሚቈጥሩን ሰዎች ላይ በድፍረት ለመናገር ቈርጫለሁ፤ እናንተን ግን በዚያ ዐይነት ድፍረት እንድናገር እንዳታደርጉኝ እለምናችኋለሁ።

3 የምንኖረው በዚህ ዓለም ቢሆንም፣ የምንዋጋው በዚህ ዓለም ስልት አይደለም።

4 ደግሞም የምንዋጋበት የጦር መሣሪያ የዚህ ዓለም መሣሪያ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ምሽግን ለመደምሰስ የሚችል መለኮታዊ ኀይል ያለው ነው።

5 በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ በትዕቢት የሚነሣውን ክርክርና ከንቱ ሐሳብ ሁሉ እናፈርሳለን፤ አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን።

6 መታዘዛችሁ በተፈጸመ ጊዜ አለ መታዘዝን ሁሉ ለመቅጣት ተዘጋጅተናል።

7 እናንተ የምትመለከቱት ውጫዊውን ነገር ብቻ ነው። ማንም የክርስቶስ በመሆኑ ቢመካ እርሱ የክርስቶስ እንደሆነ ሁሉ እኛም የክርስቶስ መሆናችንን ሊገነዘብ ይገባዋል።