1 እንግዲህ ላሳዝናችሁ ስላልፈለግሁ ወደ እናንተ ዳግመኛ ላለመምጣት ወሰንሁ፤
2 እኔ ባሳዝናችሁም እንኳ፣ ከእናንተው ካሳዘንኋችሁ በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን አለ?
3 ባለፈው ጊዜ እንደዚያ የጻፍሁላችሁ ወደ እናንተ ስመጣ ደስ ሊያሰኙኝ የሚገባቸው ሰዎች እንዳያሳዝኑኝ በማለት ነው፤ ምክንያቱም የእኔ ደስታ የሁላችሁ ደስታ እንደሚሆን አምናለሁ።
4 እንደዚያ ስጽፍላችሁ በትልቅ ሐዘንና በልብ ጭንቀት፣ በብዙም እንባ ውስጥ ነበርሁ፤ ይህንንም ያደረግሁት ለእናንተ ያለኝን ጽኑ ፍቅር እንድታውቁ በማለት እንጂ፣ እናንተን ለማሳዘን አልነበረም።
5 ማንም ሰውን ቢያሳዝን፣ ነገር ማጋነን አይሁንብኝና ያሳዘነው እኔን ብቻ ሳይሆን በመጠኑም ቢሆን ሁላችሁንም ነው።
6 እንደዚህ ያለው ሰው ብዙዎች የወሰኑበት ቅጣት በቂው ነው።
7 ደግሞም ከልክ በላይ አዝኖ ተስፋ እንዳይቈርጥ፣ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባችኋል።