21 ሰውየውም ሕልቃና ለእግዚአብሔር ዓመታዊውን መሥዋዕት ለመሠዋት ስእለቱን ለማድረስ ቤተ ሰቡን ሁሉ ይዞ ወደ ሴሎ ወጣ።
22 ሐና ግን አልሄደችም፤ እርሷም ባሏን፣ “ሕፃኑ ጡት ከተወ በኋላ፣ ወስጄ በእግዚአብሔር ፊት አቀርበዋለሁ፤ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም በዚያ ይኖራል” አለችው።
23 ባሏ ሕልቃናም፣ “መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ፤ ጡት እስክታስጥዪው ድረስ እዚሁ ቆዪ፤ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን ያጽናልሽ” አላት። ስለዚህ ሐና ሕፃኑን ጡት እስክታስጥለው ድረስ እያጠባችው በቤቷ ተቀመጠች።
24 ልጁ ጡት በተወ ጊዜ ከእርሱ ጋር አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን፣ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄትና አንድ አቍማዳ የወይን ጠጅ ወስዳ፣ በሴሎ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣችው፣ ልጁም ገና ሕፃን ነበረ።
25 ወይፈኑን ካረዱ በኋላም ልጁን ወደ ዔሊ አቀረቡት።
26 ሐናም ዔሊን እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በነፍስህ እምላለሁ፤ እዚህ ቦታ ላይ በአጠገብህ ቆማ ወደ እግዚአብሔር ስትጸልይ የነበረች ያች ሴት እኔ ነኝ።
27 ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸለይሁ፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ሰጠኝ።