1 ሳሙኤል 10:1-7 NASV

1 ከዚያም ሳሙኤል የዘይቱን ብርሌ ወስዶ፣ ዘይቱን በሳኦል ራስ ላይ ካፈሰሰ በኋላ እንዲህ ሲል ሳመው፤ “በርስቱ ላይ ገዥ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶህ የለምን?

2 ዛሬ ከእኔ ተለይተህ ስትሄድ፣ በብንያም ወሰን ላይ በምትገኘው ጼልጻህ በተባለች ስፍራ በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ። እነርሱም፣ ‘የምትፈልጋቸው አህዮች ተገኝተዋል፤ አሁን አባትህ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ፣ “ስለ ልጄ ምን ባደርግ ይሻለኛል?” እያለ በመጨነቅ ላይ ነው’ ይሉሃል።

3 “አንተም ጒዞህን በመቀጠል በታቦር እስካለው እስከ ትልቁ ዛፍ ድረስ ትሄዳለህ፤ እዚያም ሦስት ሰዎች፣ አንዱ ሦስት የፍየል ግልገል፣ ሌላው ሦስት ዳቦ፣ ሌላው ደግሞ የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል።

4 እነርሱም ሰላም ይሉሃል፤ ሁለት ዳቦ ይሰጡሃል፤ አንተም ትቀበላቸዋለህ።

5 “ከዚያ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጦር ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ጊብዓ ትሄዳለህ። ወደ ከተማዪቱ እንደ ደረስህም የነቢያት ጉባኤ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በእምቢልታና በበገና ታጅበው ትንቢት እየተናገሩ ከማምለኪያው ኰረብታ ላይ ሲወርዱ ታገኛቸዋለህ።

6 የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ይወርድብሃል፤ ከእነርሱ ጋር ትንቢት ትናገራለህ፤ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ።

7 እነዚህ ምልክቶች በተፈጸሙ ጊዜ እጅህ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና።