1 ሳኦል በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ፤ እስራኤልንም አርባ ሁለት ዓመት ገዛ።
2 ሳኦል ከእስራኤል ሦስት ሺህ ሰዎች መረጠ። ሁለቱ ሺህ በማክማስና በኰረብታማው አገር በቤቴል ከሳኦል ጋር፣ አንዱ ሺህ ደግሞ በብንያም ግዛት በጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ። የቀሩትን ሰዎች ግን ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ አሰናበተ።
3 ዮናታን ጊብዓ የነበረውን የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር መታ፤ ፍልስጥኤማውያንም ይህን ሰሙ። ሳኦልም፣ “ዕብራውያን ይስሙ!” በማለት በምድሪቱ ሁሉ መለከት አስነፋ።
4 ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጦር ሰፈር መታ፤ እስራኤልም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ርኩስ ተቈጥራ ተጠላች” የሚለውን ወሬ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ።