1 ሳሙኤል 14:1-7 NASV

1 አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፣ “ና በሌላ በኩል ወዳለው የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም ነበር።

2 ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ መጌዶን በተባለ ስፍራ ከአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ስድስት መቶ ያህል ሰዎችም አብረውት ነበሩ፤

3 ኤፉድ ይለብስ የነበረውም አኪያ በመካከላቸው ነበር። እርሱም በሴሎ የእግዚአብሔር ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፣ የፊንሐስ ልጅ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ ነበር። ዮናታን አለመኖሩን ግን ያወቀ ሰው አልነበረም።

4 ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ለመሻገር በፈለገበት መተላለፊያ ግራና ቀኝ አንዱ ቦጼጽ ሌላው ሴኔ የተባሉ ሁለት ሾጣጣ ዐለቶች ነበሩ።

5 አንዱ ዐለት በስተ ሰሜን በኩል በማክማስ አንጻር፣ ሌላው ደግሞ በስተ ደቡብ በኩል በጊብዓ አንጻር ይገኝ ነበር።

6 ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፣ “ና፤ ወደነዚያ ሸለፈታሞች ጦር ሰፈር እንሻገር፤ ምናልባትም እግዚአብሔር ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን እግዚአብሔርን የሚያግደው የለምና” አለው።

7 ወጣቱም ጋሻ ጃግሬ፣ “በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ፤ ወደ ኋላም አትበል፤ እኔም በሙሉ ልብ ካንተው ጋር ነኝ” አለው።