12 የፍልስጥኤም ጦር ሰፈር ሰዎችም፣ “ኑ ወደ እኛ ውጡ፤ አንድ ነገር እናሳያችሁ” ሲሉ በዮናታንና በጋሻ ጃግሬው ላይ ጮኹባቸው።ስለዚህ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፣ “ተከትለኸኝ ውጣ፤ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን እጅ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና” አለው።
13 ዮናታን በእጁና በእግሩ ተፍጨርጭሮ፣ ጋሻ ጃግሬውን በማስከተል ወጣ። ፍልስጥኤማውያንም በዮናታን እጅ ወደቁ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከበስተ ኋላው እየተከተለ ገደላቸው።
14 ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በመጀመሪያው ቀን ባደረጉት ግዳይ አንድ ጥማድ በምታውል የዕርሻ ቦታ ላይ ሃያ ያህል ሰዎች ገደሉ።
15 በሰፈር በዕርሻ ላይና በሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ሆነ፤ ከተማ ጠባቂዎችና አደጋ ጣዮችም ሁሉ ተንቀጠቀጡ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ሽብሩም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ነበር።
16 በብንያም ግዛት በጊብዓ የነበሩ የሳኦል ዘቦች፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት በየአቅጣጫው መበታተኑን አዩ።
17 ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች፣ “እስኪ፣ ሰራዊቱን ቊጠሩና ማን ከዚህ እንደሄደ እዩ” አላቸው። ይህን ባደረጉ ጊዜም ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም።
18 ሳኦልም አኪያን፣ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደዚህ አምጣ” አለው፤ በዚያን ጊዜ ታቦቱ በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር።