1 ሳሙኤል 14:15-21 NASV

15 በሰፈር በዕርሻ ላይና በሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ሆነ፤ ከተማ ጠባቂዎችና አደጋ ጣዮችም ሁሉ ተንቀጠቀጡ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ሽብሩም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ነበር።

16 በብንያም ግዛት በጊብዓ የነበሩ የሳኦል ዘቦች፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት በየአቅጣጫው መበታተኑን አዩ።

17 ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች፣ “እስኪ፣ ሰራዊቱን ቊጠሩና ማን ከዚህ እንደሄደ እዩ” አላቸው። ይህን ባደረጉ ጊዜም ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም።

18 ሳኦልም አኪያን፣ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደዚህ አምጣ” አለው፤ በዚያን ጊዜ ታቦቱ በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር።

19 ሳኦል ለካህኑ በመናገር ላይ ሳለ፣ በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ሁካታው እየጨመረ ሄደ። ስለዚህ ሳኦል ካህኑን፣ “እጅህን መልስ” አለው።

20 ከዚያም ሳኦልና ሰዎቹ ተሰብስበው ወደ ውጊያው ሄዱ። እነርሱም ፍልስጥኤማውያን በሰይፋቸው እየተጨፋጨፉ በታላቅ ትርምስ ላይ ሆነው አገኟቸው።

21 እነዚያ ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጐን ተሰልፈው የነበሩትና አብረዋቸውም ወደ ሰፈራቸው የወጡት ዕብራውያን ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩት እስራኤላውያን ገቡ።