1 ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ቀብቼ እንዳነግሥህ፣ እግዚአብሔር የላከው እኔን ነው፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር የመጣውን መልእክት አድምጥ።
2 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ፣ አማሌቃውያን በመንገድ ላይ ስለ ተቃወሙት እቀጣቸዋለሁ።
3 አሁንም ሂድ፤ አማሌቃውያንን ውጋ፤ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፤ አንዱንም አታስቀር፤ ወንዱንና ሴቱን፣ ልጁንና ሕፃኑን፣ የቀንድ ከብቱንና በጉን፣ ግመሉንና አህያውን ግደል።” ’
4 ስለዚህ ሳኦል ሰዎቹን ጥላኢም በተባለ ቦታ ሰብስቦ ቈጠራቸው፤ እነርሱም ሁለት መቶ ሺህ እግረኛ ወታደሮችና ከይሁዳም ዐሥር ሺህ ሰዎች ነበሩ፤