1 ሳሙኤል 16:7-13 NASV

7 እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፣ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው።

8 ከዚያም እሴይ አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር ይህንንም አልመረጠውም” አለው።

9 እሴይም ሣማን አሳለፈ፤ ሳሙኤልም፣ “እርሱንም እግዚአብሔር አልመረጠውም” አለ።

10 እሴይም ሰባቱን ልጆቹን በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር እነዚህንም አልመረጣቸውም” አለው።

11 ቀጥሎም እሴይን፣ “ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸውን?” ሲል ጠየቀው።እሴይም፣ “የሁሉም ታናሽ ገና አልመጣም፤ ነገር ግን በጎች እየጠበቀ ነው” ብሎ መለሰ።ሳሙኤልም፣ “በል ልከህ አስመጣው፤ እስኪመጣ ድረስ አንቀመጥምና” አለው።

12 ስለዚህ ልኮ አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፣ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ። እግዚአብሔርም፣ “የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው” አለው።

13 ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ፤ ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ።