1 ፍልስጥኤማውያን ሰራዊታቸውን ለጦርነት አሰባስበው፣ በይሁዳ ምድር በሰኰት ላይ አከማቹ፤ እነርሱም በሰኰትና በዓዜቃ መካከል ባለው በኤፌሰ ደሚም ሰፈሩ።
2 ሳኦልና እስራኤላውያን ተሰብስበው፣ በዔላ ሸለቆ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ለመግጠም ቦታ ቦታቸውን ያዙ።
3 ሸለቆ በመካከላቸው ሆኖ ፍልስጥኤማውያን አንዱን ኰረብታ እስራኤላውያን ደግሞ፣ ሌላውን ኰረብታ ያዙ።
4 ከጌት የመጣ ቁመቱ ከዘጠኝ ጫማ በላይ የሆነ፣ ጎልያድ የተባለ አንድ ጀግና ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጣ።
5 እርሱም ከናስ የተሠራ የራስ ቍር ደፍቶ፣ ክብደቱ አምስት ሺህ ሰቅል የሆነ የናስ ጥሩር ለብሶ ነበር።
6 በእግሮቹ ላይ የናስ ገምባሌ አድርጎ፣ በጫንቃው ላይ ደግሞ የናስ ጭሬ ይዞ ነበር።
7 የጦሩም ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የወፈረ፣ የጦሩም ብረት ስድስት መቶ ሰቅል ያህል የሚመዝን ነበር፤ ጋሻ ጃግሬውም ከፊት ከፊቱ ይሄድ ነበር።