12 ዳዊት በይሁዳ የቤተ ልሔሙ ሰው የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይ ስምንት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ በሳኦልም ዘመን ያረጀና ዕድሜው የገፋ ሰው ነበር።
13 ሦስቱ የእሴይ ታላላቅ ልጆች ሳኦልን ተከትለው ወደ ጦርነት ሄደው ነበር፤ እነርሱም ታላቁ ኤልያብ፣ ሁለተኛው አሚናዳብ፣ ሦስተኛውም ሣማ ይባላሉ፤
14 ዳዊት የሁሉም ታናሽ ነበር። ሦስቱ ታላላቅ ወንድሞቹ ሳኦልን ተከትለው ሄዱ፤
15 ዳዊት ግን የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር።
16 ፍልስጥኤማዊውም አርባ ቀን ሙሉ ጠዋትና ማታ ፊት ለፊት ብቅ እያለ ቆሞ ይታያቸው ነበር።
17 በዚህ ጊዜ እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ይህን ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር እንጀራ ለወንድሞችህ ይዘህ ወዳሉበት የጦር ሰፈር በቶሎ ድረስ።
18 ይህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፍ ለክፍል አዛዣቸው አብረህ ውሰድ፤ ወንድሞችህም እንዴት እንደሆኑ አይተህ፣ ደኅንነታቸውን የሚያረጋግጥ ምልክት ከእነርሱ ዘንድ አምጣልኝ።