1 ሳሙኤል 17:23-29 NASV

23 ከእነርሱም ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ፣ ከጌት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ፤ ዳዊት ሰማ።

24 እስራኤላውያንም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ሁሉም በታላቅ ፍርሀት ከፊቱ ሸሹ።

25 እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በየቀኑ እየመጣ እስራኤልን እንደሚገዳደር ታያላችሁ? ይህን ሰው ለሚገድል፣ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል፣ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያደርገዋል” ይባባሉ ነበር።

26 ዳዊት በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፣ “ለመሆኑ ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” ሲል ጠየቀ።

27 እነርሱም፣ “ለሚገድለው ሰው የሚደረግለትማ ይህ ነው” ሲሉ አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት።

28 ታላቅ ወንድሙ ኤልያብ፣ ዳዊት ከሰዎች ጋር ሲነጋገር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጥቶ፣ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? ትዕቢትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ፤ የመጣኸው ጦርነቱን ለማየት ብቻ ነው” አለው።

29 ዳዊትም፣ “ታዲያ ምን አደረግሁ? መጠየቅ እንኳ አልችልም?” አለ።