1 ሳሙኤል 2:12-18 NASV

12 የዔሊ ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም ነበር።

13 በዚያን ጊዜ ካህናቱ ከሕዝቡ ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚፈጽሙት ወግ ነበር፤ ይኸውም ማንም ሰው መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ሥጋው እየተቀቀለ ሳለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለውን ሜንጦ ይዞ ይመጣል፤

14 ወደ ድስቱ ወይም ወደ ቶፋው ወይም ወደ አፍላሉ፣ ወይም ወደ ምንቸቱ ይሰደዋል። ከዚያም ካህኑ ሜንጦው ያወጣውን ማናቸውንም ሥጋ ለራሱ ይወስደዋል። ወደ ሴሎ የሚመጡትን እስራኤላውያን ሁሉ የሚያስተናግዱት በዚህ ዐይነት ነበር።

15 ነገር ግን ሥቡ ገና ከመቃጠሉ በፊት የካህኑ አገልጋይ መጥቶ መሥዋዕት የሚያቀርበውን ሰው፣ “ካህኑ ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ ስለማይቀበል፣ ለካህኑ የሚጠበስ ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር።

16 ሰውየውም፣ “በመጀመሪያ ሥቡ ይቃጠል፤ ከዚያ በኋላ የምትፈልገውን ትወስዳለህ” ቢለው እንኳ አገልጋዩ፣ “አይሆንም፤ አሁኑኑ ስጠኝ፤ ያለዚያ በግድ እወስዳለሁ” ይለው ነበር።

17 ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት ይንቁ ስለ ነበር፣ ይህ የወጣቶቹ ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረ።

18 ብላቴናው ሳሙኤል ግን ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር።