1 ሳሙኤል 20:16-22 NASV

16 ስለዚህ ዮናታን፣ “የዳዊትን ጠላቶች እግዚአብሔር ይፋረዳቸው” በማለት ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።

17 ዮናታን ከፍቅሩ የተነሣ ዳዊት እንደ ገና እንዲምልለት አደረገ፤ ዳዊትን የሚወደውም እንደ ራሱ አድርጎ ነበርና።

18 ከዚያም ዮናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ነገ የወር መባቻ በዓል ነው፤ መቀመጫህ ባዶ ስለሚሆን፣ አለመኖርህ ይታወቃል።

19 ከነገ ወዲያ ምሽት ላይ ይህ ችግር በተፈጠረ ዕለት ወደ ተደበቅህበት ስፍራ ሂድና ኤዜል በተባለው ድንጋይ አጠገብ ቈይ።

20 እኔም በአንድ ዒላማ ላይ እንደሚያነጣጥር ሰው ወደ ድንጋዩ አጠገብ ሦስት ፍላጻ እወረውራለሁ፤

21 ከዚያም፣ ‘ሂድና ፍላጾቹን አምጣቸው’ ብዬ አንድ ልጅ እልካለሁ፤ ልጁንም፣ ‘እነሆ፤ ፍላጾቹ ያሉት፣ ከአንተ ወደዚህ ነው፤ ሄደህ አምጣቸው’ ያልሁት እንደሆነ፣ ሕያው እግዚአብሔርን! ክፉ ነገር አያገኝህም፤ አደጋም የለም፤ ውጣና ና።

22 ነገር ግን ልጁን፣ ‘እነሆ፤ ፍላጾቹ ያሉት ከአንተ ወዲያ ዐልፎ ነው’ ያልሁት እንደሆነ እግዚአብሔር እንድትሄድ ፈቅዶአልና ሂድ።