1 ሳሙኤል 24:8-14 NASV

8 ከዚያም ዳዊት ከዋሻው ወጥቶ ሳኦልን፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ!” ብሎ ጠራው። ሳኦልም ወደ ኋላው ዞር ባለ ጊዜ፣ ዳዊት ወደ መሬት ጐንበስ ብሎ እጅ ሲነሣው ተመለከተ፤

9 ዳዊትም ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “ሰዎች፣ ‘እነሆ፤ ዳዊት ክፉ ነገር ሊያደርግብህ ይፈልጋል’ ሲሉ ለምን ትቀበላቸዋለህ?

10 በዛሬው ዕለት በዋሻው ውስጥ እግዚአብሔር አንተን እንዴት አድርጎ በእጄ ላይ እንደ ጣለህ እነሆ፤ በገዛ ዐይንህ አይተሃል፤ አንዳንዶች እንድገድልህ ገፋፍተውኝ ነበር፤ እኔ ግን፣ ‘እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እጄን አላነሣም’ በማለት ራራሁልህ።

11 አባቴ ሆይ፤ የልብስህ ቍራጭ ይኸው በእጄ ላይ ተመልከት! የልብስህን ጫፍ ቈረጥሁ እንጂ አንተን አልገደልሁህም። አሁንም ክፋት ወይም ዐመፅ አለመፈጸሜን ዕወቅልኝ፤ ተረዳልኝም፤ እኔ ክፉ አልሠራሁብህም፤ አንተ ግን ሕይወቴን ለማጥፋት እያሳደድኸኝ ነው።

12 እግዚአብሔር በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ። ክፉ ስላደረግህብኝ እግዚአብሔር ይበቀልህ እንጂ፣ እጄስ በአንተ ላይ አትሆንም፤

13 በጥንት አባባል፣ ‘ከክፉ አድራጊዎች ክፉ ድርጊት ይወጣል’ እንደ ተባለ፤ አሁንም እጄ በአንተ ላይ አትሆንም።

14 “የእስራኤል ንጉሥ የወጣው በማን ላይ ነው? አንተስ የምታሳድደው ማንን ነው? የሞተ ውሻን? ወይስ ቁንጫ?