1 ሳሙኤል 27:1-6 NASV

1 ዳዊት ግን በልቡ፣ “ከእነዚህ ቀናት በአንዱ በሳኦል እጅ መገደሌ ስለማይቀር፣ የሚበጀኝ ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር መሸሽ ብቻ ነው፤ ከዚያ በኋላም ሳኦል በእስራኤል ሁሉ እኔን ማሳደዱን ይተዋል፤ እኔም ከእጁ አመልጣለሁ” ብሎ አሰበ።

2 ስለዚህ ዳዊትና አብረውት ያሉት ስድስት መቶ ሰዎች ተነሥተው የጌት ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ አሜህ ልጅ ወደ አንኩስ ሄዱ።

3 ዳዊትና ሰዎቹ በጌት በአንኩስ ዘንድ ተቀመጡ፤ እያንዳንዱ ሰው ከቤተ ሰቡ ጋር ነበረ፤ ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ጋር፣ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆምና የናባል ሚስት ከነበረችው ከቀርሜሎሳዊቷ አቢግያ ጋር ነበር።

4 ሳኦልም፣ ዳዊት ወደ ጌት እንደ ሸሸ በሰማ ጊዜ፣ እርሱን ማሳደዱን ተወ።

5 ከዚያም ዳዊት አንኩስን፣ “በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፣ በአገሪቱ ካሉት ከተሞች በአንዲቱ እኖር ዘንድ ስፍራ ይሰጠኝ፤ ስለ ምን አገልጋይህ ካንተ ጋር በንጉሥ ከተማ ይቀመጣል?” አለው።

6 ስለዚህ በዚያ ዕለት አንኩስ ጺቅላግን ሰጠው፤ ጺቅላግም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የይሁዳ ነገሥታት ይዞታ ሆነች።