10 እግዚአብሔርም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው።ሳሙኤልም፣ “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ።
11 እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ የሰሚውን ሁሉ ጆሮ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገር በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ።
12 በዚያም ቀን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በዔሊና በቤተ ሰቡ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ እፈጽማለሁ።
13 ዔሊ በሚያውቀው ኀጢአት ምክንያት በቤተ ሰቡ ላይ ለዘላለም እንደምፈርድ ነግሬው ነበር፤ ልጆቹ አስጸያፊ ነገር አድርገዋል፤ እርሱ ግን አልከለከላቸውም።
14 ስለዚህ ‘የዔሊ ቤት በደል በመሥዋዕትም ሆነ በቊርባን ፈጽሞ አይሰረይም’ ብዬ በዔሊ ቤት ላይ ምያለሁ።”
15 ሳሙኤል እስኪነጋ ድረስ ተኛ፤ ከዚያም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት በሮች ከፈተ፤ ራእዩንም ለዔሊ መንገር ፈራ፤
16 ዔሊ ግን ሳሙኤልን፣ “ልጄ ሳሙኤል ሆይ” ሲል ጠራው።ሳሙኤልም፣ “እነሆኝ” ሲል መለሰ።