1 በሦስተኛው ቀን ዳዊትና ሰዎቹ ጺቅላግ ደረሱ፤ በዚህ ጊዜ አማሌቃውያን ደቡቡን አገርና ጺቅላግን ወረው ነበር፤ ጺቅላግንም ወግተው አቃጥለው ነበር።
2 ሴቶቹን፣ በዚያ የነበሩትን ወጣቶችና ሽማግሌዎቹን ሁሉ ማርከው ወሰዱ፤ የማረኩትንም ይዘው ከመሄድ በስተቀር አንዱንም አልገደሉም ነበር።
3 ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ጺቅላግ እንደ ደረሱም፣ እነሆ፤ ከተማዪቱ በእሳት ጋይታ፣ ሚስቶቻቸው፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ተማርከው አገኙ።
4 በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ማልቀስ እስከሚያቅታቸው ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤
5 ሁለቱ የዳዊት ሚስቶች ማለትም ኢይዝራኤላዊቷ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢግያም ተማርከው ነበር።
6 ሰዎቹ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ነፍሳቸው ተመራ ሊወግሩት ስለ ተመካከሩ ዳዊት በጣም ተጨነቀ፤ ነገር ግን ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር በረታ።