1 ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ፣ ልጆቹን ፈራጆች አድርጎ በእስራኤል ላይ ሾማቸው።
2 የበኵር ልጁ ኢዮኤል ሲሆን፣ ሁለተኛው ልጁ አብያ ነበረ፤ እነርሱም በቤርሳቤህ ይፈርዱ ነበር።
3 ነገር ግን ልጆቹ የአባታቸውን ፈለግ አልተከተሉም፤ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ከመንገዱ ወጡ፤ ጒቦ ተቀበሉ፤ ፍርድም አጣመሙ።
4 ስለዚህ የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው ሳሙኤል ወዳለበት ወደ አርማቴም መጡ።
5 እነርሱም፣ “አንተ አርጅተሃል፤ ልጆችህ ያንተን ፈለግ አይከተሉም፤ ስለዚህ ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” አሉት።
6 ነገር ግን፣ “የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” ማለታቸው ሳሙኤልን አላስደሰተውም፤ ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤
7 እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና ሕዝቡ የሚሉህን ሁሉ አድምጥ።