1 ሳሙኤል 8:7-13 NASV

7 እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና ሕዝቡ የሚሉህን ሁሉ አድምጥ።

8 ከግብፅ ምድር ካወጣኋቸው ዕለት አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን በማምለክ ያደረጉትን ሁሉ በአንተም ላይ እያደረጉ ነው። አንተ ግን

9 የሚሉህን አድምጣቸው፤ በላያቸው የሚነግሠው ንጉሥ ምን እንደሚፈጽምባቸውም አሳውቃቸው፤ በሚገባም አስጠንቅቃቸው።”

10 ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ፣ ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ለጠየቁት ሕዝብ ተናገረ።

11 እንዲም አለ፤ “በላያችሁ የሚነግሠው ንጉሥ የሚያደርግባችሁ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሠረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፤ በሠረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ።

12 አንዳንዶቹን ሻለቆችና አምሳ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ ሌሎቹን መሬቱን እንዲያርሱና እህሉን እንዲያጭዱ፣ የቀሩትን ደግሞ የጦር መሣሪያና ለሠረገላ የሚሆኑትን ዕቃዎች እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል፤

13 ሴቶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሽቶ ቀማሚ፣ ወጥ ሠሪዎችና እንጀራ ጋጋሪዎች ያደርጋቸዋል።