12 አንድ ሰው የተቀደሰውን ሥጋ በልብሱ ዕጥፋት ቢይዝ፣ ያም ዕጥፋት እንጀራ ወይም ወጥ፣ የወይን ጠጅ ወይም ዘይት ወይም ሌላ ምግብ ቢነካ የተቀደሰ ይሆናልን?”ካህናቱም፣ “የተቀደሰ አይሆንም” ብለው መለሱ።
13 ሐጌም፣ “ሬሳ በመንካቱ የረከሰ ሰው፣ ከእነዚህ አንዱን ቢነካ፣ የተነካው ነገር ይረክሳልን?” ሲል ጠየቀ።ካህናቱም፣ “አዎን፣ ይረክሳል” ሲሉ መለሱ።
14 ከዚያም ሐጌ እንዲህ አለ፤ “ ‘ይህ ሕዝብና ይህ ወገንም በፊቴ እንደዚሁ ነው’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘የእጃቸው ሥራና የሚያቀርቡት ሁሉ የረከሰ ነው’።
15 “ ‘እንግዲህ ከዛሬ ጀምራችሁ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ከመነባበሩ በፊት የነበረውን ሁኔታ አስተውሉ።
16 አንድ ሰው ሃያ መስፈሪያ ወደ ሚሆን የእህል ክምር በመጣ ጊዜ ዐሥር ብቻ አገኘ፤ አምሳ ማድጋ የወይን ጠጅ ለመቅዳት ወደ መጭመቂያው በሄደ ጊዜ ሃያ ብቻ አገኘ፤
17 የእጃችሁን ሥራ ሁሉ በዋግ፣ በአረማሞና በበረዶ መታሁት፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም’ ይላል እግዚአብሔር፤
18 ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ፣ ይኸውም ከዘጠነኛው ወር ሃያ አራተኛ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት እስከ ተጣለበት ቀን ድረስ ያለውን ዘመን አስተውሉ፤ ልብ ብላችሁም አስቡ፤